የሠላም ስምምነቱ ሀገርና ህዝብን የጋራ ድል ባለቤት ያደረገ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንሰራለን -የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስትና በህወሐት መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ሀገርና ህዝብን የጋራ ድል ባለቤት ያደረገ በመሆኑ ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂነትና ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ላይ በማተኮር የኅይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የኪነ ጥበብ ሰዎችን ያሳተፈ ውይይት ተደርጓል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እንዳሉት÷ አስገዳጅ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ድረስ ምንጊዜም ጦርነት ለችግሮች መፍትሄ እንደማይሆን ይልቁኑም ሰላማዊ አማራጭ ሁነኛ መፍቻ መሳሪያ ነው።
እንደ ሀገር ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳትና ውድመት ያደረሰው የሰሜኑ ጦርነትን በሰላም ለመፍታት የተደረሰው ስምምነት ለህዝቡ እፎይታ የሰጠ፣ አገርን ወደ ልማት ለመመለስ ታሪካዊ ምዕራፍ የከፈተ ብለውታል።
የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍታት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ስምምነት ስለመሆኑ እና የጦርነትን ታሪክ ምዕራፍ ለመዝጋት፣ ለተጎዱ ወገኖች ለመደገፍ፣ አገራዊ አንድነት ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ከሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ሰፊ ሰራ እንደሚጠበቅ በተለይም ኅይማኖት ተቋማት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት፣ ተጎጂዎችን ወደጤናማ ሕይወት መለወጥ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በገንዘብ፣ ሃሳብና ዕውቀት በመደገፍ የጋራ ርብርብና ትጋት ይጠይቃል ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ውይይቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች አቶ ሊላይ ኅይለማርያም፣ ወይዘሮ አረጋሽ አዳነና ደበሽ ተመስገን የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ ህዝቦች ዕፎይታ እና ድል የሚሰጥ ትልቅ ደስታ የፈጠረ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተለይም የትግራይ ተወላጆች ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው÷ከጥላቻና ፉክክር ይልቅ ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርቡ ስራዎችን ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከኅይማኖት አባቶች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ አብርሐም ፣ ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ÷ የኅይማኖት ተቋማት ሁልጊዜም ለሀገርና ለህዝብ ሰላም ሲሰብኩና ሲጸልዩ እንደኖሩ አስታውሰዋል፡፡
ጦርነቱ በሰላም እንዲቋጭ የሰላም ስምምነት መደረሱ ትልቅ ብስራት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ስምምነት ሁሉም ሃይሎች ለሰላም ዕጃቸውን የሰጡበት፣ አንድ ወገን አሸናፊነት ሳይሆን አገርና ህዝብ ድል ያገኙበት፣ ኢትዮጵያ እፎይታና ፈውስ ያገኘችበት ዕድል እንደሆነም ተናግረዋል።
የኅይማኖት ተቋማት እና አባቶች የሰላም ስምምነቱ መሬት ወርዶ ገቢራዊ ይሆን ዘንድ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ዶክተር ጫኔ ከበደ እና ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው÷ የሰላም ስምምነቱን ለሀገር እረፍት የሰጠ፤ ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ወሳኝ እርምጃ አድርገው እንደሚወስዱት ገልጸዋል።
በሀገር ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ከመንግስት ጎን ቆመው የተጎዱ አካባቢዎችን ወገኖችን መልሶ ማቋቋምና ግንባታው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን በባለቤትነት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ በሌሎች አካባቢዎች ችግር የሚፈጠሩ አካላት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነም አንስተዋል።
ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት ከመስራት ባለፈ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን መደገፍ እንደሚገባ፤ ለዚህ ደግም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ተቋማዊ አሰራር እንዲዘረጋ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
የሠላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም በላይ በሰጡት ምላሸም÷ መንግስት ከጦርነቱ በፊት ጀምሮ ለሰላም ብርቱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የሰላም ስምምነቱም ተግባራዊነትም እንዲሆን ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ወደስራ መግባቱን ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውንና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፎችም ተቋማዊ አሰራር እንደተዘረጋ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መጻዒ ዕድል አስተማማኝ እንዲሆን ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ለስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም አካላት፣ ሚዲያዎችና ኪነ ጥበብ ዘርፎችም ለሰላም ሊዘምሩ እንደሚገባ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ስምምነቱን በተቀናጀ አግባብ ወደ ተግባር ለመለወጥ መሰል ውይይቶች በቀጣይ ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንዲሰፉ እንደሚደረግም ተናግረዋል።