Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ 4 ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ደቡብ ኮሪያ አስወነጨፈች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ አራት የአጭር ርቀት ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን በዛሬው ዕለት ወደ ምዕራብ የደቡብ ኮሪያ ክፍል መተኮሷ ተሰምቷል፡፡

ፒዮንግያንግ አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በጥምረት ስታካሂድ የቆየችውን በቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች የታገዘ የዓየር ኃይል ልምምድ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው ባሊስቲክ ሚሳኤሎቹን ያስወነጨፈችው፡፡

ዕኩለ ቀን ላይ የተወነጨፉት ሚሳኤሎች 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ተምዘግዝገው በምዕራባዊ የደቡብ ኮሪያ ባሕር ማረፋቸው ተነግሯል፡፡

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ትናንት ለማጠናቀቅ ቀን ቆርጠውለት ሲያካሂዱ የቆዩትን ጥምር የዓየር ኃይል የጦር ልምምድ እስከ ቅዳሜ ያራዘሙት ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ የባሊስቲክ ሚሳኤሎች አከታትላ መተኮሷን ተከትሎ ምላሽ ይሆን ዘንድ ታስቦ መሆኑን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

የጋራ ልምምዱ 240 የሚጠጉ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ፣ ሁለት ዩ ኤስ ቢ-1ቢ ስትራቴጂያዊ ቦምቦ ጣይ አውሮፕላኖች ፣ አራት ኤፍ-16 እና አራት ኤፍ-35ኤ ጀቶችን ያሳተፈ መሆኑን የደቡብ ኮሪያ ጥምር ጦር አመራሮች አስታውቀዋል።

ይህ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄዱት የተቀናጀ የዓየር ላይ የጦር ልምምድ ሀገራቱ ምንያህል የመከላከያ ጦር ዐቅም እንዳላቸው እና ለማንኛውም ዓይነት ከሰሜን ኮሪያ ለሚቃጣ ትንኮሳ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን ለማሳየት የተካሄደ መሆኑን የጥምር ጦሩ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሚያካሂዱትን ፀብ-ጫሪ የዓየር ኃይል የጦር ልምምድ እንዲያቆሙ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.