Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ እና የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷አርቲስት አሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ጥበብና ስልጣኔ እደገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ አርአያ ሆኖ ያለፈ ድንቅ አርቲስት ነው ብለዋል።

አርቲስቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቻቻልንና አብሮነትን፣ ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክሩ በርካታ የጥበብ ሥራዎችን ተቀኝቷል፤ አቀንቅኗል፤ ለሕዝብ አበርክቷልም ነው ያሉት።

ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው÷አርቲስት ዓሊ ቢራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የማይጠፋ የሀገር ባለውለታ መሆኑን አንስተዋል።

አርቲስት አሊ ቢራ በኪነ ጥበብ ስራዎቹ ፍቅርን፣ መተሳሰብን አንድነትን ለመላው ህዝባችን በማስተማር ዘመን የማይሽረው የጥበብ አሻራውን ያሳረፈ ታላቅ ባለውለታችን ነበር ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድም በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ በሙዚቃው ዓለም ድንቅ ነበር ያሉት አቶርዕሰ መስተዳድሩ÷ሐረር እና ምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚታወቁበት የፍቅር፣ የርኅራኄ፣ የጨዋነት እና የመቻቻል ምልክት እንደነበርም ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ÷በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡

አርቲስት ዓሊ ቢራ በህይወት ዘመኑ ሁሉ ለሀገሩ ሲለፋ ሲደክምና የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ የነበረ የመልካም ስብዕና ባለቤት እንደነበር አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን የገለጹ ሲሆን ÷ አርቲስቱ በዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ የሀገራችንን ባህልና እሴት እንዲሁም ፍቅርና አንድነት ማቀንቀኑን ጠቁመዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በአንጋፋው አርቲስት አሊ ቢራ ህልፈት ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በራሳቸው እና በክልላቸው መንግሥት ስም ገልጸው÷ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና ለጥበብ አድናቂዎቹ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.