የሀገር ውስጥ ዜና

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ ስንዴ ለማልማት ታቅዷል

By Alemayehu Geremew

November 07, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ ስንዴ ለማልማት ማቀዱን የዞኑ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷በተያዘው ዓመት የበጋ ወራት ኢትዮጵያ የያዘችውን ስንዴ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

አቶ መስፍን ተሾመ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስም በአርሶ አደሩ የሚነሱ የውሃ መሳቢያ ሞተር እና ሌሎች የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን የመፍታት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ከ2 ሺህ በላይ የሞተርፓምፖች ለአርሶ አደሩ ተገዝተው የማሰራጨት ሥራ መከናወኑም ነው የተጠቆሙት፡፡

በቀጣይም ለሥርጭት የተዘጋጁ ከ200 በላይ ትልልቅ የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮች መዘጋጀታቸውንም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች በበኩላቸው ÷ የበጋ ስንዴን በስፋት ለማምረት በመንግስት በኩል የሚቀርቡ ግብዓቶችን በወቅቱ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በይስማው አደራው