በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ልዩ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ 41 ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ የኢንቨስትመንት ማእድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የፅህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ መሀመድ ያህያ እንደገለጹት በ16 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት ፍቃድ እገዳ እንዲሁም በስምንት ባለሃብቶች ደግሞ የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸው መሰረዙን ተናግረዋል።
ለ17 ባለሀብቶች ደግሞ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ነው የተናገሩት።
ኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ለገቡ ባለሀብቶች የሚደረገው የድጋፍና የክክትል ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሃላፊው አስረድተዋል።
መስራት እየቻሉ ያለ አግባብ የመንግስት ይዞታዎችን ይዘው በተቀመጡ ባለሀብቶች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከክልለሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡