Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ ባላት እምቅ የተፈጥሮ ኃብት ልክ እንድታድግ የአፍሪካውያን የእርስ በእርስ ግንኙነት ሊጠናከር ይገባል- ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ ባላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ልክ እንድታድግ የአፍሪካውያን የእርስ በእርስ ግንኙነት የበለጠ ማደግ እንዳለበት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 6ኛው የአፍሪካ ኢንጂነሪንግ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት የመሰረተ ልማት ፍላጎትና አቅርቦት በፍጥነት እያደገ ነው።

አፍሪካ መልማትና መበልጸግ የሚያስችላት የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም ተባብሮ መስራት አለመቻል ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

አህጉሪቱ ያላትን እምቅ አቅም መጠቀም ትችል ዘንድ በአፍሪካውያን መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነቱ ከዚህ በላይ ማደግ እንዳለበትም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኢንጂነሮች ጉባኤ አፍሪካን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ጉልህ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፥ ይህ አይነቱ ምክክር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የሸገርና አንድነት ፓርክ ፕሮጀክቶችን በመገንባት አፍሪካውያን ኢንጂነሮች አፍሪካን መቀየር እንደሚችሉ አሳይታለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጉባኤው በኢንጂነሮች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠር የአፍሪካን የመሰረተ ልማት ግንባታ ፈጣንና ጥራት ያለው እንዲሆን ያግዛል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.