የሀገር ውስጥ ዜና

በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር በአሜሪካ ሊካሄድ ነው

By Alemayehu Geremew

November 08, 2022

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር የፊታችን ቅዳሜ በአሜሪካ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

ዝግጅቱ ለሀገራዊ ጥሪ ወገናዊ ምላሽ በሚል መሪ ሐሳብ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደሚከናወን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ኃይል መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ሳቢያ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ሰብዓዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

በዝግጅቱ ላይ በአካል መገኘት የማይችሉ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ÷ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በከፈተው ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ የሂሳብ ቁጥር 1000439142786 እና በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ የኦንላይን የገንዘብ ክፍያ አማራጭ ድጋፉን ማድረግ እንደሚችል አመልክቷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የመንግስት ተወካዮች፣አርቲስቶች፣ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱን “ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ” የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ኃይል ከተለያዩ ተቋማትና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀውም ተገልጿል።