የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ ያደረጋትን ዓለም አቀፍ የብየዳ ክኅሎት ሥልጠና የብቃት ማረጋገጫ አገኘች

By Alemayehu Geremew

November 08, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ ያደረጋትን ዓለም አቀፍ የብየዳ፣ ሥልጠና እና ቴክኖሎጂ ማዕከልነት የብቃት ማረጋገጫ ማግኘቷን የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ የብቃት ማረጋገጫውን ያገኘችው ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ የብየዳ ኢንስቲትዩት ነው፡፡

የሥራ ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የሥልጠና ብቃት ማረጋገጫ ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም በብየዳ ሙያ ለሰለጠኑ ዜጎች የሥራ ዕድልን የሚያሰፋና በዓለም ገበያ ተፈላጊነታቸውን በመጨመር በርካታ ባለሙያዎችን ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ የሙያው ባለቤቶች ለሆኑ የማዕከሉ ሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

ከፍተኛ የጥራት መስፈርቶችን አሟልታችሁ ከማዕከሉ ስልጠና በመውሰድ የዕውቀት ባለቤት የሆናችሁ ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ገበያው የሚፈልገውን ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት ለነገ የማንለው ጉዳይ በመሆኑ ተቋማችን በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡