በኢትዮ- ኬንያ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ በስኬት ተከናወነ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ- ኬንያ የኮንቨርተር ስቴሽንና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ በዛሬው ዕለት በስኬት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጁ አቶ ቴዎድሮስ አያሌው እንገደለፁት፥ በኢትዮ ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በፕሮጀክቱ ላይ የተተከሉ የተለያዩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል መሳሪያዎችንና ዕቃዎችን እንዲሁም የኮሙዩኒኬሽን ዳታ ሲግናሉን በተለያየ ጊዜ የመፈተሸ እና የመሞከር ሥራ ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰው፥ በዛሬው ዕለት ደግሞ ኃይል በማስተላለፍ ከኬንያ ጋር ያለውን ግንኙነት ያለምንም ችግር መሞከር ተችሏል ብለዋል፡፡
የሙከራ ሥራው መሳካቱ በቅርቡ ከኬንያ ጋር የሚጀመረው የኃይል ትስስር ሥራ በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚከናወን አመላካች ነው ማለታቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል።
ከቀናት በፊት የኮሙዩኒኬሽን ሲግናል በመላክ ሲግናሉን ከኬኒያ ኔትወርክ ጋር ማገናኘት መቻሉን አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮ- ኬንያ የማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ስቴሽን ፕሮጀክት በ334 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 214 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላሩ ለኮንቨርተር ስቴሽኑና ለግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመር የግንባታ ሥራ እንዲሁም 120 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ለማስተላለፊያ መስመሩ የዋለ ነው ተብሏል፡፡
የግንባታ ሥራው በ2008 የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት እስከ 2 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፍ አቅም እንዳለው በፕሮጀክቱ ሲነየር ፕሮጀክት ኢንጂነር ኃይለማርያም ሞገስ ገልፀዋል፡፡
የማስተላለፊያ መስመሩ የግንባታ ሥራ በፈረንጆቹ 2018 እንዲሁም የኮንቨርተር ስቴሽኑ በታህሳስ 2021 መጠናቀቁን ኃይለማሪያም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮ- ኬኒያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራ ሲ ኢ ቲ በተሰኘ የቻይና ኩባንያ የተከናወነ ሲሆን የኮንቨርተር ስቴሽኑና የግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመሩ ደግሞ ሲመንስ በተሰኘ ኩባንያ ተከናውኗል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል በተገነባው የኢትዮ – ኬኒያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ 994 የመስመር ተሸካሚ ታወሮች የተተከሉ ሲሆን 440 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና የዳታ ሲግናል ማስተላለፊያ ኬብሎችም ተዘርግተውለታል።