የሀገር ውስጥ ዜና

በተለያየ ምክንያት ግንባታቸው ቆሞ የነበሩ የመንገዶች ግንባታ ሥራ ተጀመረ

By ዮሐንስ ደርበው

November 09, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከወሰን ማስከበር እና ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ችግር ግንባታቸው ቆሞ የነበሩ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ፡፡

በዚሁ መሰረት÷ የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ ዐደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እና ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ ዐደባባይ – ቡልቡላ – ቂሊንጦ ዐደባባይ የሚወስደው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል።

የቃሊቲ -ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት የቀኙ መስመር የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ሥራ እና የሦስት ማሳለጫ ድልድዮች የስትራክቸር ሥራ ተከናውኖ መንገዱ በከፊል ለትራፊክ ክፍት መሆኑ ይታወሳል፡፡

ፕሮጀክቱ ባጋጠመው የፋይናንስ እና የወሰን ማስከበር ችግር የግንባታ ሥራው ተቋርጦ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ስለሆነም ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ አጋጥሞ የነበረው ችግር የቻይና ኤግዚም ባንክ ብድር እስከሚለቅ ድረስ ከመንግሥት በጀት በብድር መልክ ክፍያ እየተፈፀመ ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባስተላለፈው ውሳኔ ስለተፈታ የመንገዱ የግራ መስመር የግንባታ ሥራ ተጀምሯል፡፡

ፕሮጀክቱ 56 በመቶ መድረሱ እና እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የመንገዱን የግራ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት በማልበስ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ ፕሮጀክት 11 ኪሎ ሜትር እርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡

በተመሳሳይ ግንባታው ቆሞ የነበረው የቃሊቲ ቀለበት መንገድ ዐደባባይ – ቡልቡላ – ቂሊንጦ ዐደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል።

በአሁኑ ወቅት የድልድይ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን÷ በዚህ በጀት ዓመት ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን በማጠናቀቅ መንገዱን ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እርዝመት ያለው ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ያህሉ አስፋልት መልበሱ ተመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!