Fana: At a Speed of Life!

የ “ሄፓታይተስ” ህመም መንስዔ ፣ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሄፓታይተስ (የጉበት ቁስለት) ጉበት በተላላፊ ቫይረሶች እና ኢ-ተላላፊ አነሳሾች ምክንያት ሲጎዳ እና ሲቆስል የሚመጣ ህመም ነው፡፡

ጉበት በሆድ የላይኛው ክፍል በስተቀኝ በኩል ሲገኝ የንጥረ ነገሮችን ሂደት የሚያስተካክል፣ ደምን የሚያጣራ እና ኢንፌክሽንን የሚዋጋ ወሳኝ አካል ነው።

ስለዚህ የጉበት ቁስለት እና መጎዳት ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክ እና ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ይህን ህመም አምጪ ከምንላቸው ተላላፊ ቫይረሶች ውስጥ ሄፓታይተስ ቫይረስ ኤ፣ቢ፣ሲ፣ዲ እና ኢ ተጠቃሽ ሲሆኑ ÷ አልኮል፣ በመድሃኒቶች መመረዝ እና የሰውነት እራስን በራስ ማጥቃት ኢ-ተላላፊ ከምንላቸው ውስጥ ይካተታሉ፡፡

የሄፓታይተስ ቫይረሶች ሁሉም የጉበት በሽታ ቢያስከትሉም፥ በሕመም ክብደት፣ በስርጭት መጠን፣ በመተላለፊያ እና በመከላከያ ዘዴዎቻቸው ይለያያሉ።

ሄፓታይተስ ቫይረስ ኤ እና ኢ በቫይረሱ በተበከለ ውሃ እና ምግብ ሲተላለፉ፥ ሄፓታይተስ ቫይረስ ቢ እና ሲ ደግሞ ቫይረሱን ተሸካሚ በሆኑ ሰዎች ደም፣ በሴት ብልት ፈሳሽ፣ በዘር ፈሳሽ እና በተለያዩ የሰውነት ፈሳሾች ይተላለፋል።

የሄፓታይተስ ህመም ምልክቶች እንደ መንስኤዎች እና ህመም ክብደት በጥቂቱ ቢለያይም ድካም፣ የጉንፋን መሰል ምልክቶች፣ የሽንት መጥቆር፣ የሰገራ ቀለም መንጣት፣ የሆድ ህመም፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የክብደት መቀነስ፣ የቆዳ እና የአይኖች ቢጫ መሆን ይጠቀሳሉ፡፡

የሄፓታይተስ ቫይረሶችን ለመከላከል የሚረዱ ብዙ ክትባቶች ቢኖሩም እስካሁን የሄፓታይተስ ቫይረስ ሲ እና ኢ ክትባቶች የሉም።

ከክትባት በተጨማሪም ለቫይረሱ የመጋለጥ እድልን መቀነስ እና ሌሎች ህመሙን የሚከስቱ እንደ አልኮል እና የመድሃኒት መመረዝን መቀነስ አስፈላጊ የመከላከያ እርምጃ መሆኑን ከጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገፅ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ይህም ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ምግብን አብስሎ መመገብ፣ የግል እቃዎችን በጋራ አለመጠቀም፣ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም መጠቀም እና ከሰውነት ፈሳሾች ንክኪ መቆጠብ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.