Fana: At a Speed of Life!

ሁለት የዕደ ጥበብ ምርቶች በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት ተመዘገቡ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለት የኢትዮጵያ የዕደ ጥበብ ምርቶች በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) መመዝገባቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በንግድ ምልክትነት የተመዘገቡት የዕደ ጥበብ ምርቶችም÷ የሐረር ጌይ ሞኦት (አለላ ስፌት) እና የጋምቤላ ሉል መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ምርቶቹን በንግድ ምልክትነት ማስመዝገብ÷ ባለቤትነትን በማረጋገጥ ለማስጠበቅ እና ምርቶቹን ከፈጠራ መብት ስርቆት ለመታደግ እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ተሳታፊ ለመሆን ያስችላል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የሐረር ጌይ ሞኦት (አለላ ስፌት) ምርት በሐረሪ ክልል በሰፊው የሚመረት ሲሆን÷ በማህበረሰቡ ማንነት፣ እምነት፣ አኗኗር፣ ባህል፣ ልማድና ወግ ውስጥ የተለያየ ፋይዳ አለው፡፡

የጌይ ሞኦት 32 የሚደርሱ የስፌት ዓይነቶች እና ከ34 ዓይነት በላይ ዲዛይን ያላቸው ስነ ጥበባዊ ገፅታን የተላበሱ፣ ለስጦታ እና ለመገልገያ ይውላሉ፡፡

የማህበረሰቡ የባህል መገለጫና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው እና በአንድ የሐረሪ ሰው መኖሪያ ቤት የግድ መገኘት ስላለባቸው ምርቶቹ በማህበረሰቡ ዘንድ ልዩና ተፈላጊ ናቸው፡፡

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ምዝገባ የምስክር ወረቅት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

የጋምቤላ ሉል ምርት በጋምቤላ ክልል በሰፊው የሚመረት ሲሆን÷ ለማህበራዊ አገልግሎት የሚውል እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤት ነው፡፡

በሉል ምርት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ምርቱን ለማስተዋወቅ እና የበለጠ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኝ፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ግብዓት እንዲውል ምርቱን በዲዛይንና በደረጃ በማሻሻል የዕደጥበብ የምርቱን መለያ (ብራንድ) ምልክት በማዘጋጀት፣ በማልማት፣ በመጠበቅ ከምርቱ የሚገኘውን ጠቀሜታ ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ ሊመዘገብ ችሏል ነው የተባለው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.