የኢጋድ አባል ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት መስማማታቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢጋድ እንደ አንድ ቀጠናዊ አሐድ የኮቪድ 19ን ሥርጭት ለመግታት እና ቫይረሱ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ መሰናክል በውጤታማነት ለመከላከል ቁልፍ የመሪነት ሚናን መጫወት እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ፣ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ፣ ከጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ፣ ከኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡኹሩ ኬንያታ እና ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት በጋራ ለመሥራት መስመማማታቸውን አስታውቀዋል።
መሪዎች ለአዳዲስ እና ፈታኝ ሁኔታዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በቅርበት እና በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ከተባበርን እና በጋራ ሆነን የቀጠናውን ፍላጎት ለማስጠበቅ አመራሩ ከሠራ የቀጠናዊ ቅንጅት ግባችን አይስተጓጎልም” ብለዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision