የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ዓለምአንተ አግደው ከኤፍ ቢ አይ ረዳት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

By Shambel Mihret

November 10, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው ከአሜሪካ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ረዳት ዳይሬክተር ራይመንድ ዱዳ ጋር በሁለቱ ሀገራት የጋራ የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም አቶ አለምአንተ አግደው በኢትየጵያ የለውጥ ሥራዎች ከተጀመሩ ጀምሮ በፍትሕ ዘርፉ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን  አስረድተዋል፡፡

በፍትሕ ዘርፉ ለሚከናወኑ ሥራዎች አሜሪካ ድጋፍ ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡

ሀገራቱ በተለይም የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን፣ ሽብርተኝነትን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ሀብት መከላከልንና መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል በትብብር መሥራት እንዳለባቸው በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በፊት የተጀመሩ ድጋፎች እንዲጠናከሩ አቶ አለምአንተ መጠየቃቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ራይመንድ ዱዳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በኩል ለተደረጉ ትብብሮች አመስግነው÷ በአሜሪካ በኩል በትብብር ለመስራት ፍላጎት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰንን ጨምሮ ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡