የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል የ31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የተቋረጡ የጤና አገልግሎቶችን ማስጀመር የሚያስችል የ31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ።
ህብረቱ ድጋፉን ያደረገው የማስጀመር እና የአቅም ግንባታ ስራውን እንዲሰራ ለማስቻል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ዩኒሴፍ) ነው።
ድጋፉ የህፃናትና ሴቶችን ኑሮ ማሻሻልና በግጭቱ ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ እንዲሁም የጤና አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ከ3 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል።
በዚህ ሳቢያም ከ700 ሺህ በላይ ህፃናት መደበኛ ክትባት ጭምር ሳያገኙ ቆይተዋል ነው የተባለው።
አሁን የተደረገው ድጋፍ ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉ እና በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች የሚገኙ ሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ