በአቶ አሻድሊ ሀሰን የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ልዑክ በክልሉ ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜት ግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ የተከናወኑ ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን በጉብኝቱ ወቅት÷ ተቋሙ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል ለክልሉ አቅም የሚሆኑ ስራዎች እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በጥረትና በትጋት የማይለወጥ ነገር እንደሌለ በዚህ ተቋም የታየው ለውጥ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው÷ሌሎች ተቋማትም ተሞክሮውን ወስደው ማስፋፋት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የገጠር ቴክኖሎጂ ብዜት ግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሙስጠፋ መሀመድ በበኩላቸው÷ ተቋሙ ጥቅም ሳይሰጡ የቆዩ የተለያዩ የግብርና መሳሪያዎችን ጠግኖ ወደ ስራ በማስገባት አርሶ አደሩ በቅናሽ ዋጋ ኪራይ እንዲገለገልገልባቸው መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ የተለያዩ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው÷ የቢሮ እቃዎችን፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን አምርተን ማቅረብ እንችላለን ብለዋል፡፡
ልዑኩ ክልሉ ለበጋ መስኖ ስንዴ ስራ እያደረገ ያለውን ዝግጅት የሚያግዙ ትራክተሮችን ጨምሮ ጥቅም ሳይሰጡ የቆዩና ለምርት መሰብሰቢያ የሚያግዙ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ የግብርና መሳሪያዎችን ጠግኖ ወደ ስራ በማስገባት አበረታች ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡
ተቋሙ እንደ ቀርቀሀ አይነት የአካባቢ ምርቶችን ተጠቅሞ የሰራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡