ጆ ባይደን ከ ሺ ጂንፒንግ ጋር ሊወያዩ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ መንበረ-ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሊወያዩ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ሁለቱ ወገኖች የሚገናኙት በቀጣዩ ሳምንት ኢንዶኔዢያ ላይ በሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ ነው፡፡
ጆ ባደን እና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ከጉባዔው ጎን ለጎን በሚያካሂዱት ውይይት ሻክሮ የቆየውን የግንኙነት መስመር ለማደስ ይመክራሉ መባሉን አር ቲ ዘግቧል፡፡
የኋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ የሆኑት ካሪን ሺን ፒየር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ÷ ሁለቱ ወገኖች ሰኞ ዕለት ተገናኝተው በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በሥፋት ይመክራሉ።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ጥምር ጦር ሊቀ መንበር የሆኑት ማርክ ሚሌይ፥ ፔንታጎን ከታይዋን ጋር የሚኖረው የደኅንነት ትብብር እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሊቀ መንበሩ ዋሺንግተን ታይዋንን በጦር በመሳሪያ አቅርቦትም ሆነ በወታደራዊ ሥልጠና እንደምትደግፍ አስታውቀዋል፡፡
“ቻይና በታይዋን ደሴት ላይ በምትፈፅማቸው ጥቃቶች ዓለምአቀፋዊ የጦር የበላይነትን ለመያዝ የምታደርገውን ጥረት ታቁም” ሲሉም ነው ያስጠነቀቁት፡፡
ጆ ባይደን በታይዋን ጉዳይ ከቻይናው አቻቸው ጋር እንደሚወያዩ እና የቻይናን የ“አንድ የቻይና ፖሊሲ” ንም እንደሚያከብሩ ትናንት ገልጸዋል፡፡
ከቻይና ጋር ጤናማ “ፉክክርን እንጂ ግጭት አልፈልግም”ም ነው ያሉት።
እንደሚታወሰው በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ዋሺንግተን በታይዋን ጉዳይ ላይ ባንጸባረቀችው አቋም ተበላሽቶ ቆይቷል፡፡