Fana: At a Speed of Life!

የኮሙኒኬሽን ተቋማት የሠላም ስምምነቱን መንፈስ በመከተል መረጃዎችን ተደራሽ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከክልል እና የከተማ መሥተዳደር የኮሙኒኬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡

የውይይቱ ዓላማ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ተቋማት የሠላም ስምምነቱ መርሆችንና ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ የተግባቦት ሥራ እንዲሰራ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡

በውይይቱ ሕዝቡ ወቅታዊና ትክክለኛ የመንግሥት መረጃዎችን እንዲያገኝ በኮሙኒኬሽን መዋቅሩ መከወን ስለሚገባው ጉዳይ በተጨማሪ ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግር በሚወገድበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በአዲስ አበባ የተካሔደዉን የውይይት መድረክ የመሩት የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ÷ የሚደረጉ የመንግስት የኮሙኒኬሽን ሥራዎች የሰላም ስምምነቱን ድንጋጌዎች ያከበሩና የሕዝቦች ወንድማማችነትና አብሮነትን በሚያጠናክር አኳኋን መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት የተናበቡ፣ ትክክለኛና ወቅታዊ የመንግሥት መረጃዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን መረጃ የማግኘት ፍላጎት ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ዶክተር ለገሰ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው÷ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ተቋማት ተናብበው ከጥላቸና ግጭት ቀስቃሽ የፀዳ መረጃ ለኅብረተሰቡ በማድረስ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ተግባራዊነት እንዲያረጋግጡ አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘዉም የመንግስት የኮሙኒኬሽን ተቋማት የተጀመረውን ሀገራዊ የሰላም ሂደት ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዳው ለማድረግ መስራት አለባቸውም ብለዋል ኃላፊው፡፡

ሕዝቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግሥት መረጃዎችን በፍጥነት እንዲያገኝ፣ የሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት እንዲጎለብት፣ በግጭት ሳቢያ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ረገድ ሕዝቡ ወቅታዊ መረጃዎችን አግኝቶ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለማድረግ የተጠናከሩ የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን እንደሚሠሩም ተሳታፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መሥተዳድሮች የተውጣጡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.