Fana: At a Speed of Life!

የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚረዳ አዲስ የአሰራር ስርዓት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደሀገር በየዓመቱ በወሊድና ተያያዥ ምክንያቶች የምናጣቸውን በርካታ እናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ ረገድ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል የተባለው አዲስ የአሰራር ስርዓት ይፋ ተደረጓል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት÷ አዲሱ የአሰራር ስርዓት የእናቶችን ሞት ከቅኝት፣ ትንተና እስከ መንስኤው በጥልቀት መረጃዎችን ማቅረብ የሚያስችልና ለቀጣይ እርምጃዎችም የሚጠቁም ነው፡፡

ይህ በይፋ ስራ የሚጀምረው የአሰራር ስርዓት በቀላሉ ልንከላከላቸው በሚያስችሉ ጉዳዮች የሚሞቱትን እናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅነሳ ላይ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋልም ነው ያሉት ዶክተር ደረጀ፡፡

በተለይ በሁለት ዓመታት ውስጥ በጤና ተቋም ከሚወልዱ ከ100 ሺህ እናቶች ውስጥ የሞት ምጣኔውን 279 ለማድረስ እንዲሁም በፈረንጆች 2030 የእናቶችን ሞት ቅነሳን ከ140 እስከ 70 ለማድረስ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይም የተለያዩ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን÷ ከጤና ሚኒስቴር፣ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከተጠሪ ተቋማት፣ ከሙያ ማህበራት እና የአጋር ድርጅት ተወካዮች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.