Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታጣቂ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚያስችል ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚያስችል ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፥ በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ፣ በሀገሪቱ የልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ለማስቻል ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

በተጨማሪም በመከላከያ ሠራዊት ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የሀገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ውስጥ እንደሚገኝ፣ በዚህም አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይህንን ሪፎርም የበለጠ ለማጎልበት እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ከመከላከያ ሠራዊቱ ወቅታዊ እና የወደፊት ግዳጆች ጋር የሚጣጣም የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ የሚተካ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቷል።

የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲፋጠን ችግር ፈቺ የአቅም ግንባታ፣ የፋይናንስ፣ የማምረቻ መሳሪያ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምክር አገልግሎት፣ የማምረቻ ቦታና መሰረተ-ልማት፣ የግብዓትና የገበያ ትስስር ድጋፎች በመስጠት ማምረቻው ዘርፍ ኢንተርፕራይዞችን የማስፋፋትና የማሸጋገር ተልዕኮ ያለው ተቋም በማስፈለጉ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.