ዓለምአቀፋዊ ዜና

የፓሪስ የሠላም ፎረም ተጀመረ

By Alemayehu Geremew

November 12, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አምስተኛው የፓሪስ የሠላም ፎረም “ዘርፈ ብዙ ችግርን ማስወገድ” በሚል መሪ ሐሳብ መካሔድ ጀምሯል፡፡

ፎረሙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የሚያስከትለውን ዘርፈ- ብዙ ችግር ለመቅረፍ÷ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም ብዝሃነትን ለማጎልበት እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡

በፎረሙ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአርጀንቲናው አቻቸው አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ÷ ሩሲያ እና ዩክሬን ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ግጭቱ ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ገልጸዋል፡፡

በሀገራቱ ግጭት ምክንያት የአውሮፓ ሀገራት የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳጋጠማቸው፣ የታዳጊ ሀገራት የምግብ ዋስትናም አደጋ ላይ እንደወደቀ አስታውሰዋል፡፡

ሀገራቱ በአስቸኳይ ወደ ድርድር እንዲመጡ እና ግጭታቸውን ፈትተው ሠላም እንዲያወርዱም ጠይቀዋል፡፡

በፈረንሳይ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ዓለምአቀፋዊ ኩባንያዎች እና የፋይናንስ ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

ሉላዊነት ፣ ዓለምአቀፋዊ አስተዳደር ፣ የዓየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ሥርዓት ያለው እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ዓለምን መገንባት የሚሉት በውይይቱ ከሚተኮርባቸው ነጥች መካከል መሆናቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡