የመስኖ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ይዘረጋል-ኢ/ር አይሻ መሐመድ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸውጊዜገደብ እንዲጠናቀቁ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ይዘረጋል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂር አይሻ መሐመድ ተናገሩ፡፡
የመስኖ ፕሮጀክቶችን ዲዛይን ማድረግ፣ መገንባትና ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን የግብርና ልማቱ ላይ መሥራት ይኖርብናልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡
መስኖ እና ግብርናን ነጣጥሎ ማየት እንደማይገባ ጠቁመው÷የምንገነባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች ውኃ ይዘው ለግብርና ሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ በማድረግ በራሳችን አቅም ወደ መስኖ ልማቱ መግባት ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ፣ የጥራትና ደረጃና በተመደበላቸው በጀት በወቅቱ እንዲጠናቀቁ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት እንደሚዘረጋም አረጋግጠዋል፡፡
በማህበረሰቡ ድጋፍ፣ በተጠቃሚዎችና ተቆጣጣሪ አካላት ዕገዛ፣ በፋይናንስ ድጋፍ ሰጪና በፕሮጀክት ባለቤት ቅንጅት ፕሮጀክቶች በጊዜ፣ በጥራት፣ በውስን በጀት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱን መዘርጋት ይገባል ብለዋል፡፡
ስርዓቱ ፕሮጀክቶች ለአፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆን መንስኤ የሆኑ ጫናዎችን በመለየት ተጨማሪ ወጪን ለመቀነስ እንደሚያስችልም ማስረዳታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡