የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የድርጅቱ በአደጋ ጊዜ የደህንነትና አቅርቦት ዳይሬክተር ሾኮ ሺሞዛዋ ገለጹ፡፡
ዳይሬክተሯ በጋምቤላ ክልል በድርጅቱ ድጋፍ በመከናወን ላይ ባሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዙሪያ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል፡፡
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት÷ ድርጅቱ በክልሉ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያደረገ ባለው ድጋፍ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይ በክልሉ በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በመደገፍና በሌሎችም ዘርፎች ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ሾኮ ሺሞዛዋ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ለዜጎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
መንግስት በተለይም የስደተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለውጤታማነቱ በየደረጃው የሚገኙ አካላት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡