Fana: At a Speed of Life!

የግላኮማ መንስዔ፣ ምልክቶች እና መከላከያ መንገዶች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግላኮማ የአይን ህመም በዓይን ነርቭ ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን በዓይን ውስጥ የሚገኘው ግፊት በመጨመሩ ምክንያት የሚከሰት ነው።

የዚህ ግፊት መጨመር ደግሞ በዓይን የሚታዩ (የምናያቸውን) ምስሎች ወደ አንጎል የሚውስደውን የዓይን ነርቭ ይጎዳል፤ ይህም በቀጣይነት ቋሚ ለሆነ የዓይን ብርሃን እጦት ይዳርጋል።

በዓይን ውስጥ የሚገኘው ግፊት የሚጨምረው ደግሞ በዘር ፣ በኢንፌክሽን፣ በአይን ቀዶ ጥገና ምክንያት በፊተኛው ዓይን ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ በጤናማ ሁኔታ መንሸራሸር ሲያዳግተው ነው።

ብዙ ጊዜ በግላኮማ የሚጠቁት ከአርባ አመት እድሜ በላይ የሆኑ፣ በግላኮማ የተጠቃ ቤተሰብ ያላቸው፣ የስኳር ህመምተኞች፣ የአይን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

በአብዛኛው ግላኮማ በቅድሚያ የህመም ምልክት ላያሳይ ቢችልም ከጊዜ በኋላ ግን የመጀመሪያ ምልክት የሚሆነው በጥግ በኩል የሚጀምር የአይን ብርሃን ችግር ነው።

ከምልክቶቹ ውስጥ ድንገተኛ የሆነ የአይን ህመም፣ ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የአይን ብዥታ፣ ጥርት ያለ እይታ አለመኖር፣ የአይን መቅላት፣ የአይን ብርሃን ማጣትና የአይን እይታ ጥበት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንዲሁም ከ40 አመት እድሜ በላይ ያሉ ሰዎች በአመት አንድ ጊዜ ወደ ሃኪም በመሄድ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ማንኛውም ሰው መደበኛ የሆነ የአይን ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ማድረግ እንደሚመከር ከጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገፅ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ግላኮማ በዓለም ላይ ሁለተኛው የዓይነ ስውርነት መንስኤ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.