ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአማዞኑ መሥራች ከሐብታቸው አብዛኛውን የመለገስ ዕቅድ እንዳላቸው አስታወቁ

By Alemayehu Geremew

November 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማዞን ኩባንያ መሥራች ጄፍ ቤዞስ ከሐብታቸው አብዛኛውን የመለገስ ዕቅድ እንዳላቸው አስታወቁ፡፡

ጄፍ ቤዞስ ከተመዘገበ 124 ቢሊየን ዶላር ሐብታቸው አብዛኛውን የሚያውሉት የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመግታት እና የሰው ልጆችን አንድ መሆን ዕውን ለማድረግ ለሚሠሩ ድጋፍ ይውል ዘንድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ፎርብስ የ58 ዓመቱ የአማዞን ኩባንያ መሥራች ጄፍ ቤዞስ ከቴስላው ባለቤት እና በቅርቡ ትዊተርን የራሳቸው ካደረጉት ኤሎን ማስክ ቀጥሎ የዓለማችን ሁለተኛው ሐብታም ናቸው፡፡

ጄፍ ቤዞስ ከተመዘገበ የ124 ቢሊየን ዶላር (110 ቢሊየን ፓውንድ) ሐብታቸው አብዛኛውን ለመለገስ ዕቅድ እንዳላቸው ለ ሲ ኤን ኤን ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው ተብሏል፡፡

ቀደም ሲል ዋረን ቡፌት እና ቢል ጌትስ እንደ እነርሱ የናጠጡ የሚሏቸው የዓለማችን ሐብታሞች አብዛኛውን ነዋያቸውን ለበጎ አድራጎት ሥራ እንዲያውሉ በጀመሩት የፊርማ እንቅስቃሴ ጄፍ ቤዞን ፊት ነስተዋቸው ወቀሳ አጋጥሟቸው እንደነበርም ስካይ ኒውስ በዘገባው አስታውሷል፡፡