የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየሠራች መሆኗን ገለጸች

By ዮሐንስ ደርበው

November 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየሠራች መሆኗን የሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ተናገሩ፡፡

በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ ከሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ሚካኤል ቦግዳኖቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ዓለማየሁ በውይይቱ ላይ÷ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በመንግሥትና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት፣ መንግሥት ከለጋሾች ጋር በመተባባር በትግራይ ክልል እያካሄደ ስለሚገኘው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና የመሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ ሂደት አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆና በቀረበችባቸው ወቅቶች÷ ሩሲያ ከሀገራችን ጐን በመሰላፏ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አድናቆት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ባግዳኖቭ በበኩላቸው÷ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም መፍታታቸው የሚበረታታና ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል ማለታቸውን በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንቅስቃሴ እያደረገች እንደምትገኝም ገልጸዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ እውነታውን ዓለም እየተረዳው እንደሚገኝ ጠቁመው÷ በውይይት እንደሚቋጭ እምነታቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ሩሲያና ኢትዮጵያ ያላቸው ወዳጅነት ዘመን ተሻጋሪ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!