“ለሠላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም አዎንታዊ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል – ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሠላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም አዎንታዊ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነትን በተመለከተ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ውይይት አካሂደዋል።
የፌዴራል ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ውይይት ትኩረት ያደረገው ÷ ለሰላም ስምምነቱ በመንግስት በኩል ስለተደረገው አጠቃላይ ዝግጅት፣ የሰላም ስምምነቱ ጭብጦች፣ የስምምነቱ አጠቃላይ እንድምታ እና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ መረጃ አመላክቷል።
በውይይቱ በመንግስት በኩል ለሰላም የነበረው የወትሮ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ብሎም ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ስኬታማነት አስቀድሞ የተደረገው ዝግጅት እጅግ አመርቂ እንደነበር ተጠቁሟል።
በሰላም ስምምነቱ ጭብጦች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉም ተገልጿል፡፡
ስምምነቱ በሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የተደቀነውን አደጋ መቀልበስ የሚያስችል፣ ጦርነቱን በዘላቂነት በማቆም ዘላቂ ሰላም መገንባት በሚያስችል ሁኔታ የተፈፀመ እንዲሁም ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በጦርነቱ ቀጥታ ተጠቂ ለነበሩ የትግራይ፣ የአማራና አፋር ህዝቦች ዕረፍት የሚሰጥ መሆኑን የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ በውይይታቸው አንስተዋል።
በድምሩ ስምምነቱ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የምታቀነቅነውን ”ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን አቋም ወይም የፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤዎችን በሚያፀና መንገድ የተፈጸመ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባሕል እና የታሪክ ምዕራፍ መጀመር ያበሰረ መሆኑም ተወስቷል፡፡
ስምምነቱ እንደ ሀገር ወደ ህገመንግስታዊነት እና ህጋዊነት የሚመልስ አቅጣጫ በመያዙ እንድምታው እጅግ የላቀ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ሆኖም ግን በሰላም ስምምነቱ ደስተኛ ያልሆኑ የተለያዩ ድምጾች በየአቅጣጫው እየተስተዋሉ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም አካላት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት እና ስኬት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በጦርነት፣ በዲፕሎማሲ እና በሰላም ስምምነቱ ሂደት የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል በፖለቲካው እና በልማት ዙሪያ ተመሳሳይ ድል ለማስመዝገብ ሁሉም የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በአንድነት ሊረባረቡ ይገባል ነው የተባለው።
በከፍተኛ መስዕዋትነት የተገኘው ሀገራዊ ድል በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቅጣጫ ተቀምጧል።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በውይይታቸው፥ የሰላም ስምምነቱ ስኬታማ እንዲሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት እና ዋጋ ለከፈሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በከፍተኛ ብቃት አመራር ለሰጡት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በሰላም ንግግሩ ሂደት ተሳታፊ ለነበሩ አካላት በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
ጥላቻ፣ በቀልና የክፋት መንገድ እንደ ሀገር እንደማያዋጣን ታሪካችን ምስክር ነው ያሉት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ÷ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ቁርሾዎችና ህመሞችን ማከም፣ መጪውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የልማት፣ የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መከተል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሠላም ስምምነቱ እንዳይደናቀፍ ማድረግ ከሀገራዊ ራዕይ አኳያ መታየት እንዳለበትም የመድረኩ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው መክረውበታል ነው የተባለው ፡፡