Fana: At a Speed of Life!

በተወሰዱ ዋጋ ማረጋጋት ሥራዎች የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት እየወሰደ ባለው ገበያ የማረጋጋት ሥራ ባለፉት አራት ወራት የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመሔድ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የአቅርቦት እጥረት ባለባቸው ግብአቶች ቀጥተኛ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም አርሶ አደሩ በቀጥታ ምርቱን የሚያቀርብባቸው የእሁድ ገበያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የዋጋ ግሽበቱ እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ባለፉት አራት ወራትም የዋጋ ግሽበት መጠን እየቀነሰ መምጣቱንም ነው የጠቆሙት።

ለዋጋ ንረት መሰረታዊ መፍትሄ ምርትን ማሳደግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለሆነም ዜጎች ባላቸው ቦታ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ማምረት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከምገባ ጋር በተያያዘም 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ በመንግሥት የምገባ መርሐ-ግብር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ የምገባ ማዕከላት 30 ሺህ ሰዎች የምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

የኑሮ ውድነት መሠረታዊ መፍትሔ ምርት በመሆኑ ሁሉም በሚችለው ሁሉ በየጓሮው ማምረት ይገባዋልም ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ብክነት መቀነስ፣ ማዕድ ማጋራት፣ ማምረት፣ መታቀብ እና መምረጥን እንደ መፍትሄ ማስቀመጡንም አስረድተዋል።

በቀጣይም የገበያ ትስስሩን በማስፋት አቅርቦትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ኢትዮጵያ 6 ሺህ ሸቀጦችን ከ18 ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ ከውጭ እንደምታስገባም ጠቁመዋል።

38 አይነት ሸቀጦች ወደ ሀገር ውስጥ ዝእንዳይገቡ መከልከላቸውን በማንሳትም እነዚህ የሸቀጥ አይነቶች ባለፈው ዓመት የወጣባቸው ህጋዊ ወጪ ከ1 በሊየን በላይ ዶላር መሆኑንም አስታውሰዋል።

ይህ ዋጋም ለማዳበሪያ ከሚወጣው ወጪ ተመሳሳይ በመሆኑ እና ለሀገር ውስጥ ምርቶች ዕድል ለመስጠት፣ ምርቶቹ በከፊልም ቢሆን ለጥቁር ገበያ የተጋለጡ ስለሆኑ እንዲሁም መሠረታዊ ሸቀጦች ስላልሆኑ የሚሻለውን በመምረጥ መታገዳቸውንም ነው ያስረዱት።

በአጠቃላይ እንደሀገር ከምናገኘው የምናጣው ስለሚልቅ ለጊዜው መታገዳቸውን በመጠቆም፥ ወደፊት እንደሁኔታው ሊታይ ይችላል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.