ሰላምና ብልጽግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነትን ማስቀረት ያስፈልጋል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕግ እና ስርዓት በሀገሪቱ እንዲከበር የሚደረግ ማንኛውም ድርድር የሚጎዳ አድርጌ አለወስደውም ሲሉ ጠቅላዩ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢፌዴሪ መንግስት እና የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ያደረጉትን ድርድር በተመለከተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ “ከሰላም የምታተርፈው ኢትዮጵያ ናት፤ ሰላም ትርፋማ ናት፤ ሰላም ሚያስከፋቸው የጦርነት ነጋዴዎች ብቻ ናቸው” ብለዋል፡፡
“የሰላም መጥፎ የጦርነት ጥሩ ለውም፤ እያሸነፍክም ቢሆን ጦርነት መጥፎ ነው፤ ሰው ትገድላለህ፣ ዶላር ትተፋለህ” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያን ህልውና፣ ልዕልና እና አንድነት የሚገዳደር ነገር ሲፈጠር ግን መፋለም ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ትናንትም ነበር ነገም ይኖራል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ከዚያ በመለስ ግን መነጋገር ክፉ አይደለም፤ ድርድር፣ ንግግር ውይይት ካለም ለኢትዮጵያ እድገት ሰላም ብቻ ነው” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
በቀጣይነት በጦርነት አዙሪት የምንሽከረከር ከሆነ እንደ ሀገር እንደቅቃለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለሰላምና ለብልፅግናችን ስንል ነው ጦርነትን ማቆም ቀዳሚ ምርጫችን የምናደርገውም ብለዋል፡፡
ሰላም ማለት ግን የጦርነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን ህግና ስርዓትን ማክበርም ነው፤ ሕግ እና ስርዓት በሀገሪቱ እንዲከበር የሚደረግ ማንኛውም ድርድርም የሚጎዳ አድርገው እንደማይወስዱ ነው የተናገሩት።
አሸባሪ ከተባለ ሃይል ጋር መነጋገር ሰላም እስካመጣ ድረስ፤ ሽብር ማስቀጠል እስካልሆነ ድረስ ክፉ አይደለም ሲሉም አመልክተዋል።
ከድርድር በኋላ በመተማመን እጦት እና ቃል የተገባውን ካለመፈፀም ድርድሮች እንደሚበላሹ አንስተው፥ ለዚህም በዓለም 154 ድርድሮች የከሸፉት ከተስማሙ በኋላ ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው መሆኑን ጥናት እንዳመላከተ አንስተዋል፡፡
“እኛ አንድ እርምጃ ሄደናል ፣ተወያይተናል፣ ተስማምተናል፣ ፈርመናል፤ ቀጥሎ የሚጠበቅብን የገባነውን ቃል መፈፀምን ሰላማችንን ዘላቂ ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡
ይህም ችግር አልባ እንዳይደለ እና ችግር እንዳይገጥም መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከወልቃይት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ ደግሞ “ብዙ ሽረባዎች እንዳሉ አውቃለው፤ በዚህ ሽረባ ውስጥ የመንግስት እጅ የለበትም ፤ አንዳንድ ሰዎች የፌደራሉ መንግስት እያሉ ብዙ ሽረባዎች ይሰራሉ፤ ሂደቱን ላለማበላሸት ነው ዝም ያልነው፤ ሂደቱ መስመር ሲይዝ ለህዝቡ እናሳውቃለን” ብለዋል፡፡
በፕሪቶሪያ የተደረገው ውይይትም ወልቃይት የማን ይሁን በሚለው ላይ ለመወሰን የተደረገ እንዳይደለ በማንሳት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ግን ንግግር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በፌቨን ቢሻው