ተሰርዞ የነበረው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የእጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ በደረሰ የወንጀል ጥቆማ ምክንያት ተሰርዞ የነበረው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የማውጣት ስነ ስርዓት ተካሄደ፡፡
በዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ 25 ሺህ 791 የ40/60 እና 20/80 ቤቶች ዕጣ እየወጣባቸው እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
በዕጣው በ20/80 መርሐ ግብር 18 ሺህ 930 ቤቶች እና በ40/60 ደግሞ 6 ሺህ 843 ቤቶች ናቸው የተካተቱት፡፡
በተጨማሪም ነባርና በ2005 ዓ.ም የባለሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎችን ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ 300 ቤቶችን ቀሪ ስራ በማከናወን ነባርና አዲስ ተመዝጋቢዎች በእጣው ተካተዋል፡፡
በዕጣው በአጠቃላይ 146 ሺህ 892 እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በቂ ቁጠባ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 93 ሺህ 352 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 53 ሺህ 540 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ብቁ የሚሆኑትም የ20/80 (ስቱዲዮ፣ ባለ 1 እና ባለ 2) ነባር ተመዝጋቢዎች (1997) በመመሪያው መሠረት ዝቅተኛውን የ60 ወራት ቁጠባ መጠን እንዲሁም የባለ 3 መኝታ ነባርና አዲስ ተመዝጋቢዎች (2005) ዝቅተኛውን የ84 ወራት ቁጠባ መጠን ያሟሉ ናቸው፡፡
የ40/60 ተመዝጋቢዎችን ከ40 በመቶ እና ከዚያ በላይ ቁጠባ ያላቸው ለእጣ ውድድር ብቁ የሆኑ እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ማለትም መረጃ መውሰጃ የመጨረሻ ቀን፣ መሰረት መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ከባንክ በተገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ የመረጃ ማጥራት ኮሚቴው ባጠራውና ባደራጀው የመጨረሻ ሰነድ መሰረት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡