Fana: At a Speed of Life!

የቤት ዕጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዓቱን ፍትሐዊነትን በሚያሰፍን መልኩ ለማከናወን ጥረት ተደርጓል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሐዊነት ጥያቄ ይነሳበት የነበረው የቤት ዕጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዓት በአዲስ መልክ የሚመለከተው አካል ተሳትፎበት ለቀጣይም ፍትሐዊነትንና ግልጸኝነትን በሚያሰፍን መልኩ ለመስራት የምንችለውን ሁሉ ጥረት አድርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል የተለያዩ አማራጮን በመዘርጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዛሬ እድለኛ ለመሆን ለተዘጋጁ ቆጣቢዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ከንቲባዋ÷በፈተናዎች ውስጥ በርካታ ድሎችንና ውጤቶችን እያስመዘገብን ዛሬ ላይ መድረስ ችለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“ዛሬ ዕጣ የሚወጣባቸው ቤቶችም በርካታ ችግሮች፣ በለውጡ ዋዜማ የስራ ተቋራጮች ስራውን ጥለው ከመጥፋት ጀምሮ የመሰረተ ልማት ዝርፊያ፣ የግንባታ ጥራት ችግር፣ የፋይናንስ እጥረት፣ የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናርና ሌሎችም ችግሮች በተወሳሰበ ሂደት ውስጥ እንድናልፍ አድርገውናል” ነው ያሉት።

የከተማ አስተዳደሩ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ከንግድ ባንክ በመበደር በብዙ ውጣ ውረድ ችግሮችን በመፍታትና ክትትል በማድረግ ቤቶቹ ለዕጣ ብቁ እንዲሆኑ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የቤቶቹ ዕጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዓት ባጋጠመ የሌብነትና የማጭበርበር ምክንያት ከዚህ በፊት ዕጣ ለማውጣትና ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የተደረገው ሂደት መደናቀፉን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ የተጠረጠሩትን ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕ እንዲሰፍንና የህዝብን ሀብትና ንብረት ከዘራፊዎች ለመታደግ ስራዎች መሰራተቸውንም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.