ባልተመጠነ ድምጽ ምክንያት ዓለም ላይ 1 ቢሊየን ወጣቶች ለመስማት ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናት አመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለማችን 1 ቢሊየን የሚሆኑ ወጣቶች ድምጽ መጥነው ባለማዳመጣቸው ለመስማት ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች አመላከቱ፡፡
አብዛኛው ወጣቶች በስልኮቻቸው አማካኝነት ሙዚቃ ሲያዳምጡም ሆነ ፊልሞችን ሲመለከቱ የጆሮ ማዳመጫ ይጠቀማሉ።
ኤም ጂ ግሎባል ኸልዝ የተባለው መፅሔት ባወጣው መረጃ ከ12 እስከ 34 አመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊና ወጣቶች በአብዛኛው ይህን ሲያደርጉ እንደሚስተዋሉ ይጠቅሳል።
የጥናቱ ባለቤት ሎረን ዲላርድ እንደሚናገሩት ከመጠን ላለፈ የሙዚቃ ወይም የፊልም ድምጽ መጋለጥ በጆሮ ውስጥ የሚገኙ የስሜት ሕዋሳትን እና አወቃቀሮቻቸውን ሊያዳክም ይችላል፡፡
ከፈረንጆቹ 2000 እስከ 2021 በተለያዩ አካባቢዎች ሶስት የመረጃ ቋትን በመጠቀም ጥናቱ እንድተደረገም ነው የተገለጸው።
በጥናት ውጤቱም በርካቶች ሙዚቃ በስልካቸው ሲያዳምጡም ሆነ ፊልሞችን ሲመለከቱ ከፍተኛ የድምጽ መጠን መጠቀማቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከ92 ጀምሮ እስከ 112 ዴሲብል (የድምጽ መጠን መለኪያ) መጠን እንደሚጠቀሙ የጥናት ውጤቱ አመላክቷል።
ይህ ከመጠን ያለፈ ድምፅ የማዳመጥ ልምድ ለረጀም ጊዜ የሚደጋገም ከሆነ በጀሮ ውስጥ የሚገኙ የስሜት ህዋሳትን በመጉዳት የመስማት ችግርን እንደሚያስከትልም ነው የተገለፀው፡፡
በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶችም ከጆሮ ማዳመጫዎች ባለፈ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የሙዚቃ ድግሶች እንዲሁም የምሽት መዝናኛ ቤቶች ላልተመጣጠነ ድምጽ ያጋልጣሉ በሚል የተለዩ ናቸው።
የመስማት ችግርን መከላከል እና ለህዝብ ጤና ቅድሚያ መስጠት ይገባል የሚለው ጥናቱ የተመጠነ ድምፅ እንዲኖር ፖሊሲዎችን ማውጣት እና መተግበር አስፈለጊ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ሙዚቃ ተመራጭ መዝናኛ ቢሆንም ደህንነቱ በተጠበቀ እና በተመጠነ ድምፅ ሙዚቃዎችን ማዳመጥ እንደሚገባ መገለፁን ሲ ኤን ኤን አስነብቧል፡፡