በጁገል ዙሪያ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚሠራው ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጁገል ውስጥና ዙሪያ የሚከናወኑ ሕገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጠብቆ ለትውልድ ከማስተላለፍ አኳያ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን ገምግመዋል፡፡
በዚህም ከሃብት አሰባሰብ፣ ከፅዳትና ውበት እንዲሁም ከሕገ-ወጥ ግንባታና መሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር መገምገማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
አቶ ኦርዲን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ለማስተላለፍ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው÷ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጎልበት እና ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ መሥራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በተለይም በጁገል ውስጥና ዙሪያ የሚከናወኑ ሕገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከቅርሱ ጋር በተያያዘ ከዘመቻ በመውጣትና ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!