Fana: At a Speed of Life!

ሰላም ለንግዱ ማህበረሰብ ቁልፍ ሚና አለው- አቶ ታዬ ደንደአ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላም ለንግዱ ማህበረሰብ ቁልፍ ሚና አለው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደአ ገለጹ፡፡

“ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬት የፋይናንስ  ተቋማትና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚና ” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ሚኒስትር ዴዔታ ታዬ ደንደአ እንደገለጹት÷ሰላም ለንግዱ ማህበረሰብ ቁልፍ ሚና አለው፡፡

ብሄራዊ መግባባት ከሌለ ፓለቲካው ይታመማል ያሉት አቶ ታዬ ደንደአ÷ የፖለቲካው መታመም ደግሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮችን በማወክ ቀውስ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ የሚታከመው በምክክር መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም ላይ ሁሉም በመሳተፍና ምክክሩን በማሳካት ዘላቂ ሰላም መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሀገሪቱ ላይ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝም ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ የሀገሪቱ ብሄራዊ ምክክር መሰረታውያን፣ ንድፈ ሀሳቦች፣ ልምዶችና ሀገሪቱ ያለችበት ደረጃ እንዲሁም ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬት የፋይናንስና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚና በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡

ውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስቴርና የኢንሼቲቭ አፍሪካ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች የተውጣጡ  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

በዘቢብ ተክላይ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.