በመዲናዋ ከ246 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞችን የሚያሳትፍ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ246 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞችን የሚያሳትፍ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ፡፡
የ2015 የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ በሚሊኒየም አዳራሽ አስጀምረውታል።
በክረምት ወራት ሲሰሩ የቆዩ የበጎ ፈቃድ ስኬቶችን በበጋም ለመድገም ያስችል ዘንድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ የበጋ በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በይፋ ወደተግባር መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴው ከ246 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን እንደሚያሳትፍ ተገልጿል።
በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ353 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡
3 ሺህ ቤቶችን በማደስ አረጋውያን፣አካል ጉዳተኞችን የሀገር ባለውለታዎችን ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፥ በዚህም ሰውን ከመደገፍ እና ከማገዝ ባሻገር ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የመንግስትን ወጪ ማዳን እንደሚቻል መገለጹን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ̎በጎ ፍቃደኝነት አያጎድልም፣ ሁሉም ነገር በመንግስት በጀት ሊሰራ አይችልም̎ ብለዋል፡፡
̎በዚህ ስራ የምትሳተፉ ዜጎች ጉልበታችሁ ወርቅ ነው ፤በጎ አስተሳሰባችሁ ከገንዘብ በላይ ነው̎ ሲሉም ገልጸዋል፡፡