ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አቋርጦት የነበረውን የኩላሊት ንቅለ ተከላ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በኮቪድ-19 ምክንያት አቋርጦት የነበረውን የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ሆስፒታሉ አቋርጦት የነበረውን የህክምና አገልግሎት ዳግም የጀመረው ከመስከረም 18 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሆስፒታሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳለው ፥ አገልግሎቱን ለመጀመር ያሰበው ቀደም ብሎ ቢሆንም በነበረበት የመድሀኒት አቅርቦት ችግር እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ አግልግሎቱን መስጠት ሳይቻል ቆይቷል፡፡
ከመስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ለአምስት ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንደተካሄደም ሆስፒታሉ ገልጿል።
በሆስፒታሉ በአመት ከ 50 እስከ 60 ለሚደርሱ ሰዎች አግልግሎቱን ለመስጠት መታሰቡም ነው የተመለከተው።
በትዕግስት አስማማው