ጀርመን ለሴፍቲ ኔት እና ግጭት ማገገሚያ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አስታወቀች
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በጀርመን ኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር የአፍሪካ ዳይሬክተር ቢሪግት ፒከል ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም በኢፌዴሪ መንግስት እና በህወሓት መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት እና በሀገራቱ የልማት አጋርነት ዙሪያ መክረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እና ተጨባጭ ውጤቶችን ለማሳየት ቁርጠኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
በጀርመን ኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር የአፍሪካ ዳይሬክተር ቢሪግት ፒከል በበኩላቸው፥ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አድንቀው ለዘላቂ ሰላም ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል።
አያይዘውም የሰላም ስምምነቱ ዋጋ እንዲታወቅ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ፣ ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እና ተጠያቂነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።