Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ከተሰማሩ ግዙፍ የቻይና ኩባንያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ ግዙፍ የቻይና ኩባንያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

ምክክሩ ኩባንያዎቹ በምርት ሂደት ላይ እያጋጠሟቸው ስላሉ ችግሮች እና በመንግስት ህግ እና ፖሊሲዎች ላይ ላላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እና ምክክር ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በውይይቱ፥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት  ኮምሽነር ለሊሴ ነሜ፣ የገንዘብ ሚኒስትር  ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰው እንዲሁም የኢንቨስትመንት  ምክትል ኮምሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ከባለሀብቶቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ በመሰረተ ልማት፣ ፋይናንስ፣ ፀጥታ ፣ አገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም በህግ እና ፖሊሲ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም በሁሉም የመንግስት መዋቅር የማስተካከያ ስራ እንደሚሰራም አቅጣጫ  አስቀምጠዋል፡፡

ሁለቱም ተቋማት በጋራ ጠንካራ የሆነ የድጋፍ እና ክትትል ስራን እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች ሚኒስትር ኮንስላር ያንግ ይሃንግ በበኩላቸው፥ የቻይና መንግስት የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ እድገት በመደገፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት አስረድተዋል፡፡

በቻይና ባለሀብቶች እና በመንግስት መካከል ግልፅ የሆነ ግንኙነት እና ትብብር መፍጠር ለሚከሰቱ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ከማስቻሉ ባሻገር የቻይና ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ላይ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው መግለፃቸውንም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.