Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ በራይድና የታክሲ አገልግሎት በሚሰጡ ሹፌሮች ላይ የሚፈፀም ግድያን በተመለከ ያካሄደውን የምርመራ ውጤት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር በራይድና የታክሲ አገልግሎት በሚሰጡ ሹፌሮች ላይ የሚፈፀም ግድያንና የከባድ ውንብድና ወንጀልን በተመለከ ያካሄደውን የምርመራ ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡

በራይድና በሌሎች የትራንስፓርት አገልግሎት ዘርፍ  ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በሚረዱ አሽከርካሪዎች ላይ ባለፉት ሁለት አመታት በተለያየ ጊዜ አሰቃቂ ወንጀሎች እንደተፈጸሙ ተጠቅሷል፡፡

የምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳየው፥ በራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ሹፌሮች ላይ የወንጀል ተግባሩን የሚፈፅሙት የውንብድና ቡድን አባላት አብዛኛውን ጊዜ ወንጀሉን ከመፈፀማቸው በፊት የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል ነው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ ባቱ መስመር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የትራንስፓርት አገልግሎት እንዲሰጣቸው ያደርጋሉም ተብሏል፡፡

አገልግሎቱን ወደሚያገኙበት አካባቢ ሹፌሮቹን በመውሰድ እና አንዳንድ ጊዜም አዲስ አበባ በሚገኙ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች በምሽት በመውሰድ ሹፌሮቹን ለሽንት አቁሙልን በማለት ካስቆሙ በኋላ ወንጀሉን እንደፈጸሙም በምርመራ ግኝቱ ተረጋግጧል፡፡

አሽከርካሪዎችን በጋራ በመሆን በስለት በመውጋት፣ በገመድ አንገታቸውን በማነቅና በሽጉጥ ተኩሰው በመግደል አስከሬናቸውን በመጣል ተሽከርካሪዎቹንና ሌሎች ንብረቶችን እንደሚወስዱም ተገልጿል፡፡

የወሰዷቸውን ተሽከርካሪዎች አይነታቸውን በመቀየር፣ ታርጋ በመለጠፍ ለሽያጭ የሚያቀርብ ሌላ የተደራጀ ቡድን መኖሩንም የምርመራ ውጤቱ ጠቅሷል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በዚህ የውንብድና ቡድን ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹን ወንጀል ፈፃሚዎችንና በውንብድና ተግባር የተወሰዱ ተሽከርካሪዎችንም በቁጥጥር ስር አውሏል ተብሏል፡፡

ወንጀሉን በተደራጀ ሁኔታ ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎችን በመያዝ ከተደራጀው 9 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 6 መዝገቦችን በማጠናቀቅ በ12 ተከሳሾች ላይ እስከ ሞት ፍርድ ድረስ በሚያስቀጣ በከባድ የውንብድና ወንጀልና በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ክስ መመስረቱም ተገልጿል፡፡

በቀጣይም ምርመራቸው እየተከናወኑ በሚገኙ መዝገቦች ላይ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ አጥፊዎችን በሕግ የማስጠየቅ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሹፌሮች በቡድን በመሆን አገልግሎት በሚጠይቁ ሰዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልም ተብሏል፡፡

በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠትና መሰል ክስተቶችም ሲያጋጥሙ ማህበረሰቡ አገልግሎቱን ለሚሰጡ ሹፌሮች ድጋፍ እንዲያደርግ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.