Fana: At a Speed of Life!

5ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የማምረቻና የቴክኖሎጂ ንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ተከፈተ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 5ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የማምረቻና የቴክኖሎጂ ንግድ ትርዒት ዛሬ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤን ጨምሮ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቱ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እና በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚከናወንበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

መንግስት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ የተከፈተው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢትም ለኢትዮጵያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ የገበያ ትስስር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር ረገድ ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው፥ የንግድ ትርኢቱ በማምረቻው ዘርፍ ለተሰማሩ አምራቾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አያይዘውም እንደነዚህ አይነት የንግድ ትርኢቶች መዘጋጀታቸው የሀገር ገፅታን ለመገንባትና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ አላቸው ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቱ ላይ ከ100 በላይ የሀገር ውስጥና የውጪ አምራች ኩባንያዎች፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ አምራቾችና አስመጪዎች እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ተሳታፊ ናቸው።

ዓለም አቀፉ የንግድ ትርኢት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ለጎብኚዎች በነፃ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.