ሕገ ወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠር አመራሩ በቅንጅት እንዲሠራ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ሕገወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎችን በመቆጣጠር ምርቱ ለአገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲውል ሁሉም አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ፡፡
በማዕድን ሀብት እና በ2015 ዓ.ም የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በዲማ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የውይይቱ ዓላማ በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ ያሉትን ችግሮች መቅረፍና መቀጠል የሚገባቸውን በመለየት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ማሳደግ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ሕገወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎችን በመቆጣጠር የወርቅ ምርት ለአገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለማዋል ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው አመራር ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት በቅንጅት እንዲሠራ ሲሉ አሳስበዋል።
በክልሉ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የወርቅ ማዕድን እየተመረተ ቢሆንም÷ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የምርት መጠን በእጅጉ ቀንሷል መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት በ1ኛው ሩብ ዓመት ከ264 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱ እና በተያዘው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ግን 32 ኪሎ ግራም ብቻ ማስገባት መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
በክልሉ የሚመረተውን የወርቅ ማዕድን መጠን ከፍ ለማድረግም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት ተመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!