የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ ለድጎማ ይወጣ የነበረን ወርሃዊ ወጪ ከ10 ቢሊየን ብር ወደ 4 ቢሊየን ዝቅ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ መንግስት ለድጎማ ያወጣው የነበረውን ወርሃዊ ወጪ ከ10 ቢሊየን ብር ወደ 4 ቢሊየን ብር ዝቅ ማድረጉን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት በነዳጅ ማደያዎች ላይ በተጣለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው፡፡
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት÷ ከሶስት ወራት በፊት ተግባራዊ የሆነው የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ በዘርፉ እምርታ እያመጣ ነው።
ለአብነትም መንግስት በየወሩ በነዳጅ ድጎማ ይደርስበት የነበረውን ኪሳራ ከ10 ቢሊዮን ወደ 4 ቢሊየን ብር መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።
መንግስት እስካሁን በነዳጅ ድጎማ 179 ቢሊየን ብር ዕዳ ወይም ኪሳራ እንዳለበት ጠቅሰው÷ የድጎማው ሂደቶች እየተስተካከሉ ሲመጡ ቀስ በቀስ ዕዳውን መቀነስ ያስችለዋል ብለዋል።
መንግስት ለነዳጅ ግዥ የሚያወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ እንደ ፖሊሲ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ማበረታቻዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዳጅ ተደራሽነት ላይ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።
በዚህም ነዳጅ በሚያመላልሱ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችና ነዳጅ ማደያዎች ላይ ቴክኖሎጂዎችን በመግጠም ቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር እየተሰራ እንደሆነ መነጋራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መንግስት ከዓለም የነዳጅ ገበያ ዋጋ አንጻር አሁንም ድጎማ እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ÷ ለአብነትም በዓለም አቀፍ ዋጋ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ ናፍታ 81 ብር፤ ቤንዝን ደግም 66 ብር በሊትር ይሸጥ ነበር ብለዋል።
ከድጎማ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በታሪፍና መሰል ጉዳዮች ላይ አሁንም በተለይ በክልል ዋና ዋና ከተሞች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለስልጣኑ ከክልሎች ጋር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።