በሩብ ዓመቱ 50 ሚሊየን የሚጠጋ ብር እና 17 ኮንቴነሮች ተወረሱ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 49 ሚሊየን 868 ሺህ 465 ብር፣ 2 ተሽከርካሪዎች እና 119 ሺህ ዶላር ግምት ያላቸው 17 ኮንቴነሮች በመንግሥት ተወረሱ፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ጽ/ቤት ኃላፊ በረከት ማሞ እንደገለጹት÷ በሩብ ዓመቱ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ፣ በሙስና ወንጀል የተመዘበሩ የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ከማስመለስ እና የፍትሕ አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ከሕግ ማስከበር ጋር በሩብ ዓመቱ 7ሺህ 891 መዛግብት በፖሊስ ምርመራቸው ተጣርቶ እንደቀረቡ ጠቅሰው÷ በ7 ሺህ 789 መዛግብት ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች እንደተሰጠባቸው ተናግረዋል፡፡
በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ፣ በሙስና እና በኢኮኖሚ የወንጀል ዓይነቶች፣ በተደራጁ የኢኮኖሚና የሙስና ወንጀል ዓይነቶች፣ በሀገሪቱ በተለያዩ ሥፍራዎች በነበሩ ግጭቶች የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ምርመራ ማካሄድን ጨምሮ በርካታ የወንጀል መዝገቦች ላይ ክርክር ተካሂዶ ብያኔዎች መሰጠታቸውን አብራርተዋል፡፡