የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ሙስጠፌ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

By Shambel Mihret

November 18, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታይለር ቤክለማን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን እና በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሴን ጆንስ ተሳትፈዋል፡፡

በውይይታቸውም በክልሉ በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ድርቅ ዘላቂ መፍትሔ በማምጣት የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ÷ በክልሉ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሚሰጠውን ዕርዳታ በማጠናከር የህብረተሰቡን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን÷ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተለይም በሶማሌ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ የምናደርገውን ተሳትፎና ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።