Fana: At a Speed of Life!

”አገራዊ ፍቅርን በማስቀደም ኢትዮጵያን ማገልገል ይገባል” – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ”አገራዊ ፍቅርን በማስቀደም ኢትዮጵያን ማገልገል ይገባል” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በመገኘት ሥልጠና እየወሰዱ ለሚገኙ የመካከለኛ እና ነባር ዲፕሎማቶች ያላቸውን ተሞክሮ እና ልምድ አካፍለዋል ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ታታሪነት ለዲፕሎማሲ ስራ ቁልፍ በመሆኑ በማንኛውም ሁኔታ ጤናማ እና ገንቢ ግንኙነት መመስረት ይገባል ብለዋል ።

አገራዊ ፍቅርን በማስቀደም ኢትዮጵያን ማገልገል እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቷ አካታች የስራ ባህሎች በመለማመድ ሴቶችን በመስኩ ማብቃት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ውይይቱን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን÷ በቂ የሰው ሀይል እና ተገቢ መዋቅር በማጠናከር የዲፕሎማሲ መርህን በመከተል የኢትዮጵያን አገራዊ ጥቅም ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ የመማሪያ መድረክ እና መለስተኛ የስልጠና እቅድ በማውጣት ዲፕሎቶች ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው÷ አገራዊ ጥቅምን ማዕከል በማድረግ በሁሉም ተሳትፎን ማጠናከር እንደሚገባና የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያን ማገልገል እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመውሰድ በርትቶ መስራት እና አገር እና ህዝብን ማገልገል እንደሚገባ አስረድተዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.