Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ሩሲያን የቆየ ግንኙነት በኪነ ጥበብና በባህል መስኮች ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የሩሲያን የቆየ ወዳጅነትና ግንኙነት በኪነ ጥበብና በባህል መስኮችም ማሳደግ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ለሩሲያ ባህላዊ ሙዚቃ ቡድን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ነው።

ሩሲያ ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ ፈታኝ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን የተናገሩት አቶ ቀጀላ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለረጅም ዘመናት በመጠበቅም በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ፣ በትምህርት እና በዲፕሎማሲ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ሀገራቱ ካላቸው ታሪካዊ እና ማህበራዊ ትስስር አኳያ በኪነ ጥበብና እና በባህል ዘርፎች በትብብር በመስራት የህዝብ ለህዝብ ትስስራቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

የሩሲያ የባህላዊ ሙዚቃ ቡድን አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን እና የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች የተለያዩ ዝግጅቶችን ያቀረበ ሲሆን÷ ይህን መሰሉ ዝግጅት በሁለቱ ሀገራት መካከል የባህል እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት አቶ ቀጀላ ።

የሩሲያን ብሔራዊ ቀን አስመልክቶ የተካሄደው ይህ ዝግጅት የሩሲያን እና የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማጠናከርን አላማው ያደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጀኒ ተረኺን ተናግረዋል።

የባህል ቡድኑ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በዛምቢያ እና በታንዛኒያ ዝግጅቶቹን ማቅረቡን አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል።

በወንድወሰን አረጋኸኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.