Fana: At a Speed of Life!

የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ መንስኤ፣ ምልክቶችና የመከላከያ መንገዶች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ በጭንቅላት ውስጥ ያሉ ሴሎች ኦክስጅን እንዳያገኙ በማድረግ እና በሰውነት ውስጥ በቂ የደም ዝውውር እንዳይኖር በማድረግ የሚከሰት ህመም ነው።

እጅግ በጣም አሳሳቢ ሲሆን÷ የአካል ጉዳት እና ሞትን ከሚያስከትሉ በሽታዎች አንዱ ነው ።

ሁለት አይነት የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ አይነቶች ሲኖሩ አንዱ Hemorrhagic ወይም የሚደማ በጭንቅላት ውስጥ ደም ሲፈስ ወይም አርተሪዎች ተጎድተው ደም ወደ ውጪ በመፍሰሱ ምክንያት የሚከሰት አይነት ነው።

ሌላው Ischemic ወይም የኦክስጅን እጥረት ሲሆን የደም ዝውውር ሲገታ ወይም መተላለፍ ሳይችል ሲቀር እና በቂ ኦክስጅን ወደ ሰውነት መዘዋወር ባለመቻሉ ምክንያት የሚከሰት አይነት መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የበሽታው ምልክቶች ራስ ምታት፣ የእጅ / የእግር መዛል፣ መድከም፣ ፓራላይሲስ የተወሰነ የሰውነት ክፍል አለመንቀሳቀስ ወይም ለመራመድ መቸገር፣ ለመናገር የአፍ መተሳሰር ወይም ቃላት ለማውጣት መቸገር እና የፊት መጣመም ይጠቀሳሉ፡፡

በሽታው የመከሰቻ ምክንያቶች ደግሞ ዋነኛው የደም ግፊት በሽታ ሲሆን የደም ግፊት ፤ የስኳር ፤ የልብ፣ የኮልስትሮል ህመም ያለባቸው ሰዎች መድሃኒታቸውን በአግባቡ ካለመውሰድ ወይም በማቋረጣቸው ምክንያት ለስትሮክ ይጋለጣሉ።

ሌላው የአልኮል መጠጥ አዘውትሮ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የሆርሞን መዛባት መከሰት፣የእድሜ መግፋት መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የበሽታው መከላከያ መንገዶች ደግሞ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት መከተል እንደ ቅባት ጮማ የበዛባቸውን ምግቦች አለመመገብ፣ የአልኮል መጠጥ አለመውሰድ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ እንደ ደም ግፊት፣ የስኳር፣ የልብ፣ የኮልስትሮል ህመም ያለባቸው ሰዎች መድሃኒታቸውን በሕክምና ባለሙያዎች ትዕዛዝ መሰረት በአግባቡ መውሰድ ይጠቀሳል፡፡

ምልክቶቹ ከታዩም በአቅራቢያ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት በመሄድ የምርመራ የጤና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በዓለም ላይ በየሁለት ሰከንዱ አንድ ሰው በስትሮክ ሕመም እንደሚጠቃ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.