በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሌማት ትሩፋት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በግልገል በለስ ከተማ የሌማት ትሩፋት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ተካሄደ።
በመርሐ ግብሩ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰንና ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ አሻድሊ ሃሰን በመርሐ ግብሩ እንደገለጹት÷ ክልሉ የተቸረውን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም የሌማት ትሩፋቱን ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል ።
የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሰን በበኩላቸው÷ የሌማት ትሩፋት የስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የውጭ ንግድ ለማሳለጥ፣ ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር ዋና አላማው መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
መርሐ ግብሩን በፋይናንስና በሙያ መደገፍ አንደሚገባም ገልጸው÷ለዚህም አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
የሌማት ትሩፋት በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራስንለመቻል የሚደረገውን ጥረት ያፋጥናል ያሉት ደግሞ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ናቸው፡፡
በመርሐ ግብሩም በክልሉ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጎብኝተዋል።
በሌላ በኩል የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር 300 የውሃ ፓምፖችንና 60 ትራክተሮችን ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስረክቧል።
ድጋፉን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን አስረክበዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ