Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት በጦርነት ለወደሙ ትምህርት ቤቶች የሚውል የ33 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል እና ለተማሪዎች ምገባ የሚውል የ33 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ጦርነቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች 8 ሺህ 500 ትምህርት ቤቶች መውደማቸውና 1 ሺህ 500 ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ፥ 2 ሚሊየን የሚደርሱ ህፃናት  ከትምህርት ገበታቸው ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሰላም ስምምነቱ በሚደረገው ጉዞ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

ድጋፉ የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የምገባ ፕሮግራም፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ የጤና እና መሰል አገልግሎት ለተማሪዎች ተደራሽ በማድረግ ጥራት ያለው ትምህርትን ለመተግበር የሚደረገውን ጉዞ ያግዛል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከህብረቱ ጋር በጋራ እንደሚያስፈፅሙት ተጠቁሟል።

በድጋፉ 80 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን÷ 60 ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ተጠቁሟል።

በቅድስት አባተ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.