የሀገር ውስጥ ዜና

የሌ/ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ሐውልት እና በስማቸው የተሰየመ ትምህርት ቤት ተመረቀ

By Shambel Mihret

November 22, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ሐውልት እና በስማቸው የተሰየመ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ተመርቋል።

ሐውልቱን እና ትምህርት ቤቱን የመረቁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የትውልዱ የሃገር ወዳድነት፣ የጀግንነትና የፅናት ተምሳሌት ነው ብለዋል።

የሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የጀግንነት ታሪክ የኢትዮጵያ ጀግንነት ታሪክ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አብዲሳ አጋ ዓለም ዓቀፍ ኢትዮጵያዊ ጀግና ሆኖ ሳለ በሚገባው ልክ ያልተዘመረለት ጀግና መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ውርስ ስለሰንደቅ አላማ ክብር በፅናት መቆም፣ ኢትዮጵያን በየትኛውም ጥቅም አሳልፎ አለመስጠት፣ በየትኛውም ጫና ውስጥ ኢትዮጵያውያን የማንንበረከክ ህዝቦች መሆናችንን በተጨባጭ ማረጋገጥ፣ ነፃነትና አልበገር ባይነት የሉአላዊነታችንና የኢትዮጵያዊነታችን መለያ  መሆኑ ነው ብለዋል፡፡